የልዕለ ሐምራዊ ጨረራ (Ultraviolet radiation) ምንድነው?

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ፤ በተለይ በአዲስ አበባ ተመዘገበ የተባለው እጅግ ከፍተኛ የልእለ ሐምራዊ ጨረራ አመልካች (UV Index) የልኬት መጠን በብዙኅን ዘንድ መነጋገሪያ ከመሆንም ባሻገር  አንዳንድ ት/ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ከዚህ ጨረራ ለመጠበቅ በክፍላቸው ውስጥ እና በጥላዎች ስር የምሣ ሰዓታቸውን እንዲያሳልፉ እየመከሩ ይገኛሉ።

ለመሆኑ ይህ መረጃ ምን ያህል እውነት ነው? የልእለ ሐምራዊ ጨረራ አመልካች ምንድነው? እውን የልእለ ሐምራዊ ጨረራ በሰው ልጆች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት አለ? የልእለ ሐምራዊ ጨረራ አመልካች መጠን መጨመሩ ምንን ያመለክታል? የልእለ ሐምራዊ ጨረራ አመልካች መጠን በጨመረ ጊዜ ምን ማድረግ አለብን? የልእለ ሐምራዊ ጨረራ መጨመር እና የሙቀት መጠን ግንኙነት አላቸው? የሚሉትን ሐሳቦች በዝርዝር እንዳስሳለን።

የልዕለ ሐምራዊ ጨረራ (Ultraviolet radiation) ምንድነው?

ፀሐያችን የምትለቀው ብርሃን በዘርፉ ባለሙያዎች ነጭ ብርሃን (white light) በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህ ብርሃን የመሬታችንን ከባቢ አየር በሚያገኝበት ግዜ ወደ ተለያዩ የኤሌክትሮ-መግነጢሳዊ እስፔክትረም (Electromagnetic Spectrum) ይበተናል። የልእለ ሐምራዊ ጨረራ 10 በመቶ የሚሆነውን የኤሌክትሮ-መግነጢሳዊ እስፔክትረም ይሸፍናል።

የልእለ ሐምራዊ ጨረራ አመልካች (UV Index) ምንድነው?

የልእለ ሐምራዊ ጨረራ አመልካች ፀሐይ በሰማይ ላይ ከፍተኛ በሆነችበት ጊዜ (በእኩለ ቀን አካባቢ) ወደ ምድር ገጽ ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀውን የልእለ ሐምራዊ ጨረራ በምን ያህል መጠን የሰውነታችንን ቆዳ እንደሚጎዳ የሚያሳይ ትንበያ ነው።

የልእለ ሐምራዊ ጨረራ አመልካች ፤  እ.አ.አ. በ1994 የአሜሪካው ብሔራዊ  የአየር ንብረት አገልግሎት እና የአሜሪካ አካባቢያዊ ጥበቃ ኤጀንሲ አማካኝነት ለመጀመሪያ ግዜ ሊረቅ ችሏል።  ዜጎች ከቤት ውጪ ለሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን በማሰብ ይህንን አመልካች (Index) በቁጥሮች በመከፋፈል ዜጎች ዕለታዊ የልእለ ሐምራዊ ጨረራ መጠንን በቀላሉ እንዲረዱ ከዛም ባለፈ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል ። ከዚህ በታች የምትመለከቱት ምሥል የልእለ ሐምራዊ አመልካች ቁጥሮች ምን እንደሚያመለከቱ ያሳያል።

ምድር ላይ የሚደርሰው የልእለ ሐምራዊ ጨረራ መጠን በዋነኛነት በሰማዩ ላይ ካለው የፀሐይ ከፍታ፣ በማዕከላዊው ከባቢ አየር (Stratosphere) ውስጥ ካለው የኦዞን መጠን እና ከዳመና ሽፋን መጠን ጋር የተያያዘ ነው። ይሁን እንጂ የደመና ሽፋን ሁል ግዜ የልእለ ሐምራዊ ጨረራ መጠንን ይቀንሳል ማለት አይደለም። ለዚህም እንደ ማሳያ ጥቅጥቅ ያለ ደመና የልእለ ሐምራዊ ጨረሮችን መጠን በእጅጉ ሲቀንስ አንዳንድ ሥሥ የደመና ሽፋኖች የልእለ ሐምራዊ ጨረራ መጠንን  የደመና ሽፋን በማይኖርበት ግዜ ካለው የጨረራ መጠን ሊያስበልጡ  ይችላሉ። 

ሀገራችን ኢትዮጵያ በጂዖግራፊያዊ አቀማመጧ ምክንያት ለምድር ወገብ የቀረበች በመሆኗ ፤ በዓመት ሁለት ግዜ ማለትም በወርሃ ነኅሴ እና ወርሃ ሚያዝያ ከፍተኛውን የጨረራ መጠን ታገኛለች።

ከታች ባለው ምሥል እንደምንመለከተው የምድር ወገብ ከሌሎቹ የሰሜናዊ እና ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ አካባቢዎች አንፃር ከፍተኛውን የልእለ ሐምራዊ ጨረራ ያገኛል። 

በሃገራችን ከፍተኛው ወቅታዊ የልእለ ሐምራዊ ጨረራ መጠን በዓመት ውስጥ ሁለት ግዜ ይከሰታል። ይህ ከፍተኛ የልእለ ሐምራዊ ጨረራ ሊፈጠር የቻለው ምድራችን በምህዋሯ ፀሐይን በምትዞርበት ግዜ የፀሐይ ብርሃን የምድር ወገብን በቀጥታ የሚያገኝበት ወቅት ሁለት ግዜ በመሆኑ ምክንያት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በምድር ወገብ አካባቢ ከሌሎቹ የመሬት አካቢዎች በተለየ መልኩ የዖዞን ሽፋን መሸንቆር እና መሳሳት የራሱን ጉልህ ሚና ይጫወታል። ከታች የምትመለከቱት ሠንጠረዥ በነዚህ ሁለት ወራት ሃገራችን ባለፉት አምስት ዓመታት የነበራትን የልእለ ሐምራዊ ጨረራ አመልካች ያሳያሉ።